Saturday, May 9, 2015

የግንቦት ወሬ (ክፍል ሁለት)



የግንቦት ወሬ (ክፍል ሁለት)
(ውብሸት ታደለ)
የዘንድሮው ምርጫ ለቀልድ አዋቂ ሰው በሳቅ የሚገድል ጨዋታ ነው፡፡ እንደኔ ዓይነቱ ቀልድ የማያውቅ ጅላጅል ግን ኢህአዴግን እንደፓርቲ ቆጥሮ በኢህአዴግ ድርጊት ሲቃጠል ይውላል፡፡ መቼም ኢህአዴግ ፖለቲካን የሚመለከተው በልጅነታችን እንደምንሰራቸው የመንደር ተንኮሎች ነው፡፡ ተንኮል መስራት ያልበሰሉ ጭንቅላቶች ሙያ እንደሆነ ለማወቅ ከልጅነታችን በላይ ምስክር የለም፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች በሚሰሩት የልጅ ተንኮል ከመሳቅ ይልቅ የምበሳጨው ለምንድነው? ኢህአዴግ ማለት 24 ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያን ሲገዛ የመሪዎቹ ዓላማ በግልፅ የማይታወቅ ድርጅት መሆኑ ጠፍቶኝ ነው? ቀድሞውኑ አገሬን አጥንት እንዳዬ ጉንዳን ሊቀራመቷት መነሳታቸው ጠፍቶኝ ነው ወይ? ለምንድነው በቀልዳቸው የማልዝናናው? በአገር መቀለድ ብርቅ ነው እንዴ? እንደነዚህ ዓይነት ጥያቄዎች አዕምሮዬን ቢሞሉትም በቀልዳቸው ግን አልስቅም፡፡ ለምን?...

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለስልጣን ሲሉ የስልጣን ተቀናቃኝን ማሰርና መግደል በየገፁ የምናነበው ሃቅ ነው፡፡ ስልጣንን ለማስጠበቅ ሲባል ልጆችን ለተቀናቃኝ ወገን ከመዳር ጀምሮ ተቀናቃኝን እስከማሰር ብሎም እስከመግደል የሚደርሱ እርምጃዎች እንደነበሩ አንብበናል፡፡ ይህ እውነት ለአውሮጳ ታሪኳ ለአፍሪቃ ደግሞ ዜናዋ ነው፡፡ ነገር ግን አፍሪቃ አዳዲስ ዜናዎችን ማሰማት ጀምራለች፤ ወደናይጀሪያ በኩል የሰማነው አዲስ ዜናም የዚሁ አካል ነው፡፡ እኛ ግን ግንቦት 20 ላይ እንደቆምን ነን፡፡ አሁንም ስልጣን በጠመንጃ እንጅ በሰለጠነ ፖለቲካ የማይገኝ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የምርጫ ኮረጆ የወያኔዎቹ ጥይት ማዘያ ከረጢት ሆኗል፡፡ ይህን የጅል ጨዋታ የማወራው ድሮውንስ እነጅቦን ስለማላውቃቸው ነው? ድሮስ ቢሆን የ2007 ኢትዮጵያ ወደ 1997 ኢትዮጵያ ታድጋለች ብዬ ነው? ወይስ እነጅቦ ሃብታቸውን አሽሽተው ጨርሰዋል ብዬ ነው? ይህ ሁሉ ባይጠፋኝም በቀልዳቸው ግን አልስቅም፡፡ ለምን?...

ኢህአዴግ ሰዎችን ማሰር የእጅ ሰዓት እንደማሰር የሚቀለው ድርጅት ቢሆንም ለአቅመ እስር የበቁ ነቄ ልጆች ግን አሁንም በየመንደሩ አሉ፡፡ ብርቱካንን ሲያስር ርዕዮት፣ ርዕዮትን ሲያስር ማህሌት፣ ማህሌትን ሲያስር ወይንእሸት፣ ወይንእሸትን ሲያስር…፡፡ ኢትዮጵያ ነቄ ልጆች ቢያንሷትም አላጣችም፡፡ በ(ዣን)ጥላ ስር የተሰባሰቡ ልጆች ሰማያዊ ቀለም ተቀብተው መጥተዋል፡፡ እነጅቦም ጥላ ይዞ የሚራመድ ሰው ባዩ ቁጥር የሚገቡበት ይጠፋቸዋል፡፡ እንዲያውም ፀረ-ጥላ መሆናቸውን ተከትሎ “ጥላ-ቢስ” የሚል መጠሪያ ወጥቶላቸዋል አሉ፡፡ በየመንደሩ ወሬ ሲቃርሙ የሚውሉ ካድሬዎችን ለመግለፅ “ጥላ-ቢስ” ከሚል ቃል በላይ የት ይገኛል?! በነገራችን ላይ ህግ ማውጣት የሚወዱት ሟቹ ጠቅላያችን በህይወት ቢኖሩ ኖሮ ጥላ መያዝንና ሰማያዊ ቀለም መጠቀምን በህግ ይከለክሉት ነበር፡፡ በፓርላማው ተገኝተውም ህጉ እንከን የማይወጣለትና በውጭጭ የተኮረጀ መሆኑን ይናገሩ ነበር፡፡ አንቀፆቹን ልገምት…

ጥላ ወዳዱ የአገው ህዝብ ከአሁን በኋላ በጥላ ምትክ ዱላ እንዲይዝ…

ዓይነ-ጥላ፣ ጆሮ-ጥላ፣ ጥላሸት፣ ወንድም ጥላ፣ ጥላ-ቢስ፣ ወዘተ. የተሰኙ ቃላትን የተጠቀመና ለመጠቀም ምክንያት የሆነ፤ ከተጠቀመው ሰው ጋር አብሮ የነበረ አዋጁን እንደጣሰ ይቆጠራል…

“ጥላ ቆርቆሮ ፋብሪካ” ድርጅቱን በጥላ ስም የሰየመ በመሆኑ በጥላ አራማጅነት ተፈርጇል፡፡ በመሆኑም “ጥላ ቆርቆሮ”ን የገዛ፣ የሸጠ፣ ያሻሻጠ፣ ሲሸጥ ያየ፣ ወዘተ. አዋጁን እንደጣሰ ይቆጠራል…

ሰማያዊ ቀለም የተቀቡ ቤቶች፣ “በሰማያት የምትኖር” የሚለው የፀሎት ቃል፣ “የሰማዩ አሞራ” በሚል የሚጀምረው ግጥም፣ ወዘተ. ላይ ማስተካከያ ሳይደረግባቸው ጥቅም ላይ ያዋላቸው ሰው አዋጁን እንደጣሰ ይቆጠራል…

ሟቹ በህይወት ቢኖሩና ይህ ህግ ቢወጣ ኖሮ እስቅ ነበር? ጅቦቹ የሚያመጡት ጨዋታ ሁሉ የማያስቀኝ አስቂኝ ስላልሆነ ነውን? ወይስ በአገር ላይ ሲቀለድ ስቄ አላውቅም? ያም ሆነ ይህ በቀልዳቸው አልስቅም፡፡ ለምን?...

ምክንያቱም…

ቀናትን በሳቅ ማለፍ የሚቻለው ነገ ሌላ ቀን እንደሚሆን ሲታሰብ ነው፡፡ ጭቆና ግን ዛሬህን ብቻ ገድሎ የሚያቆም ነገር አይደለም፡፡ ጦሱ ጊዜን ተሻጋሪ ነው፡፡ የደርግ ግፍ የጎዳት የያኔዋን ኢትዮጵያን ብቻ አይደለም፡፡ ደርግ የዚያን ትውልድ ህይወትና የዚህን ትውልድ ወኔ ገድሎ ነው ያለፈው፡፡ ዛሬ ጅቦቹ የሚዘሩት ግፍስ ነገ ምን ሆኖ ይበቅላል ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በዘርና በሆድ ላይ የተዘራ ፖለቲካ ፍሬው ምን ይሆናል ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ የሚያሳስበኝ የጅቦቹ አለመሄድ ሳይሆን በጊዜ አለመሄዳቸው ነው፡፡ በእያንዳንዱ ቀን የሚሰሩት ግፍ ሲሰላ ለጥቂት ጊዜ በዚሁ ከቀጠሉ ከዚያ በኋላ ሄዱም አልሄዱም ትርጉም አልባ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እንደአገር ለመቀጠል የሚያስችለን ሰንሰለት ይበጠሳል፡፡ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” የሚባለው ያኔ ነው፡፡ ጅቦቹ ከሄዱ በኋላ መጮህ ነገን አይታደግም፡፡ 

አሁን ጊዜው የጩኸት ነው፤ የለቅሶ ነው፡፡ ፈፅሞ የሳቅ ጊዜ አይደለም፡፡ ዛሬያችንን ገድለውታል፤ ነገአችንን እንዳይደግሙት እንጩህ፡፡…

ከግንቦት ሰማይ ጋር አብረን እናጉረምርም፡፡

(ይቀጥላል)

Monday, May 4, 2015

የግንቦት ወሬ /ክፍል አንድ/



የግንቦት ወሬ /ክፍል አንድ/

(ውብሸት ታደለ)

ግንቦት እየመጣ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ግንቦት የዝንብ እና የንብ ወቅት ነው፡፡ ዝንቡ በራሱ ስልጣን፣ ንቡ በገዢዎቻችን ትዕዛዝ አካባቢያችንን ይቆጣጠራሉ፡፡ ከቤታችን በር ላይ ከቆመ የመብራት ግንድ ላይ የንቢቱ ስዕል ተለጥፏል፡፡ ይህን ስዕል የሳለው ሰው እንደ አንዳንድ ሰዓሊዎች ድብቅ መልዕክት ማስተላለፍ የፈለገ ይመስለኛል፡፡ የንቢቱ ቅልጥም የMHDን¹፣ ውፍረቷ ደግሞ የአባዱላን ሰውነት የሚወክል ሲሆን ይህም የድርጅቱን የአበላል ታሪክ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ የገበሬው ንብ ከሲታና ለስዕል እንኳን የማትበቃ ስትሆን የድርጅቱ ንብ ግን 24 ዓመት በደንብ የተቀለበች የሀረር ሰንጋ ነች፡፡ ለመሆኑ ንቢቱ እንዲህ የደለበችው አበባ ከዬት አግኝታ ነው? ገዢዎቻችን ንቢቱ አበባውን ያገኘችው ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ እንደሆነና አፍቃሪዋም ገበሬው እንደሆነ ቢናገሩም ህዝቡ ግን ንቢቱ የደለበችው ስኳር እየላሰች² ነው ይላል፡፡ የሆነው ሆኖ ኢህአዴግ ከዝንብ ጋር በግንቦት የመጣ ድርጅት በመሆኑ ዝንብን ምልክት ቢያደርግ የበለጠ ምክንያታዊ ይሆን ነበር፡፡ በዚያ ላይ ለቆሻሻ ግብሩ ዝንብ እንጅ ንብ አትመጥነውም፡፡ ለንቢቱ ማማለያ አበባን ምልክታቸው ያደረጉ ፓርቲዎችም ዝንቢቱን ለመግደያ ጭራን ምልክታቸው ያደርጉ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ቅንጅት በ1997 ምርጫ ሁለት ጣትን ምልክት ካደረገ በኋላ የተለያዩ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክታቸውን በተለያዩ ጣቶች ዙሪያ ወስነዋል፡፡ የቀረው ብቸኛ ጣት የመሃል ጣት ሲሆን እርሱንም ለብልግና ቅርብ የሆኑ ወጣቶች ለቀጣይ ምርጫ ምልክት እንደሚያደርጉት ዝተዋል፡፡

በግልፅ ለመነጋገር፣ ኢህአዴግን ከንብ ጋር የሚያገናኙት ብቸኛ ነገሮች የመናደፍ ልማዱና ለስካር (ለጠጅ/ለቢራ) ቅርብ መሆኑ ነው፡፡ የነቁትን በዱላ፣ ያልነቁትን በቢራ እየዘረረ አገሪቱን እየገዛ ነው፡፡ በዳሽን ከፍታ ላይ የትውልድ ስካር ታውጇል፡፡ በቃሊቲ ሸለቆ ውስጥ የትውልድ እንባ ተቁሯል፡፡ የጊዜው ዘፈን “ኧረ ንቦ አትናደፊ” ቢሆንም ንቢቱ ግን ከመናደፍ አልቦዘነችም፡፡ እንደውሻ ንብ መርዟን እንጅ ማሯን ቀምሰነው አናውቅም፡፡ ከአበቦች ቀስም ይልቅ የእኛ እምባ ይጣፍጣታል፡፡ ፃድቁ አቡዬ ለፅድቅ ሲሉ እምባቸውን ለወፍ እንዳጠጡት እኛም ለመሰንበት ስንል እምባችንን ለንቢቱ እያጠጣን ነው፡፡ የኢትዮጵያ እናቶች ጡታቸውንም ዓይናቸውንም እያጠቡ ነው፡፡
   
ያም ሆነ ይህ ግንቦት የበራሪ ነፍሳት እና የፖለቲካ ወር ነው፡፡ ከግንቦት ልደታ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ህዝብ በሰፊው የሚታወቁ ቀናት ግንቦት ሰባት እና ግንቦት ሃያ ናቸው፡፡ በግንቦት ልደታ የሚጀመረው የልደት ንፍሮ ክረምቱን ሙሉ በሚዘልቅ የሞት ንፍሮ ይታጀባል፡፡ አደባባዩ በህዝብና በጥይት ጩኸት ይሞላል፤ ጌቶቹም ይህን ልዩ የሙዚቃ ስልት እያዳመጡ የሙዚቃው አቀናባሪ የጥይቱን ድምፅ ከፍ እንዲያደርገው ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡ በእነበረከት አስተሳሰብ ጠብመንጃ የሙዚቃ እንጅ የጦር መሳሪያ አይደለም፡፡ ሰልፈኛውን ለመበተን ፌዴራል ፖሊስ ለምን አስለቃሽ ጭስ አይጠቀምም የሚል የዋህ ጥያቄ ሰዎች ሲያነሱ እሰማለሁ፡፡ መልሱ ግልፅ ነው፤ ሰልፈኛው ቀድሞውኑ እያለቀሰ ነው የሚኖረው፤ እያለቀሰ ነው የሚሰለፈው፡፡ በዚህ ሁሉ መሃል ገዢዎቻችን ጥቁር ሳቃቸውን ይስቃሉ፡፡ ከንቧ ይልቅ ለቀፎዋ ቅርብ የሆነውን አስተሳሰባቸውን ይዘው በዚህ ዘመን ህዝብን በዱላ መግዛት ይፈልጋሉ፡፡ አገር በሚያገማ የዘር ፖለቲካ ታውረው፣ ድንቁርናን እንደርዕዮተ-ዓለም ተቀብለው፣ አገሪቱን እንደዶሮ ስጋ ቆረጣጥመው በሏት፡፡ በነገራችን ላይ፣ ንብ ብሄሯ ምንድነው?

ኢህአዴግአውያንን በዚህ ሰዓት ከሚያስጨንቋቸው ነገሮች ዋናው የቀለም አብዮት ነው፡፡ የዘመኑ ሴቶች ስማቸውን እንደሚቀይሩት ዓይነት የስም ለውጥ ያደረገው በግብር ግን ያልተቀዬረው ኢቲቪ በጉዳዩ ላይ መቀባጠር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ የቀለም አብዮትን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የፖለቲካ ተንታኞች ከፖለቲካ ሳይንስ ይልቅ ለቀለም ቅብ ወይም ለስዕል ጥበብ ቅርብ የሆኑ ይመስለኛል፤ ከአብዮቱ ይልቅ ቀለሙ ላይ ቢያተኩሩ መልካም ነው፡፡ በብሄራዊ ደህንነት ስም ዜጎችን ማረድና ማዋረድ አዲስ የጭቆና ስልት አይደለም፤ ደርጎቹም በትዝታ የሚያወጉን ያንኑ ነው፡፡ የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ህዝብን መግደልና ማሰቃዬት ምን ዓይነት የደህንነት ፍልስፍና ነው?! 

ግንቦት እየመጣ ነው …

ግንቦት ሃያ እየመጣ ነው …

ከዚያ በፊት ደግሞ ግንቦት ሰባት እየመጣ ነው፡፡

ህዝቡ ግን “ግንቦት ሰባት… ግንቦት ሰባት” ሲል የሚውለው የምርጫው ቀን መቀዬሩን አልሰማም እንዴ? ወይስ ህዝቡ ራሱን ማሸበር ጀመረ? ይህን ጉዳይ ማጣራት የገራፊዎቻችን ድርሻ ነው፡፡ የአብዮቱ ስም ቢጫ እንዲሆን የጠቆምከው ወዳጄ! ምክንያትህን ለማጠናከር ከውሃ ጀሪካን ሰልፍ ባሻገር የዘይት ጀሪካን ሰልፍ ተጀምሮልሃልና ደስ ይበልህ፡፡ አብዮቱም የሚነሳው ለዘይት ሰልፍ በወጣው ህዝብ እንደሚሆን አትጠራጠር፡፡ 

ግንቦት የሙቀት ወር ነው፡፡ አየሩም ፖለቲካውም ይሞቃል፡፡

ግንቦት የማጉረምረም ወር ነው፡፡ ሰማዩም ህዝቡም ያጉረመርማል፡፡

የምወራረድበትን እውነት ግን ልናገር- አብዮቱ በፍፁም አይቀርም፡፡ ምክንያቱም፣ ኢቫን ፓቭሎቭ³ እንደፃፈው there’s something called Freedom Reflex! ነፃነትን መሻት ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ተፈጥሯዊው እውነት ኢትዮጵያዊም እውነት የማይሆነው ደግሞ ኢትዮጵያውያን ሰው ሰራሽ ከሆኑ ብቻ ነው፡፡ “We Need Freedom. Freedom! Freedom! Freedom!!!”

(ይቀጥላል)

¹ Mengistu Hailemariam Dessalegn (ዘላለም ክብረት ከእስር ቤት በፃፈው ደብዳቤ ላይ ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም ደሳለኝን ለመጥራት የተጠቀመበት ቃል)
² የቀድሞው (የአሁኑም) ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የድሮ ጓዳቸው ሙስና እንደበላ ለመግለጽ የተጠቀሙበት ቃል
³ ከዲዮጋን ቀጥሎ በውሻው ዝነኛ የሆነ ሊቅ፤ ከራሱም በላይ ውሻው ዝናኛ የሆነ፡፡ “የፓቭሎቭ ውሻ” ሲባል አልሰማችሁም?!

Tuesday, February 14, 2012

ለፍቅሬ (5) (የቫላንታይን ቀን መታሰቢያ)

ተኩስ ነው ፍቅር፡፡ እያንዳንዳችን የሰብዕናችንን ምላጭ እሳብን በየመንገዱ ሰው እንገድላለን፡፡ ምላጩን ስንስብ አይታወቀንም፡፡መገዳደል ብቻ፡፡ ‘በፍቅር ገደለኝ’ ይል የለ ሀበሻ ?! ሟች እንደታዳኝ አውሬ እየተንፈራፈረ ስጋውን ለአዳኝ ጥርስ ይገብራል፡፡ ምኞቱን ይገብራል፡፡ ህይወቱን ይገብራል፡፡
ፍቅሬ፡ ባህላችን ለቁርጥና ክትፎ ክብር አለው፤ ከኔ ወዲያ ቁርጥ! ይሄው ብይኝ!! ለቁርጥ የሚሆን ቀይ ስጋ በቀይ ልብስ አጊጠሸ ተመገቢ፡፡ ጥንዶች ሁሉ ለቀይ ስጋ መታሰቢያነት በቀይ ቀለም የሚያጌጡበት ቀን ነው ዛሬ፡፡ የሰው ልጅን በላኤ-ሰብነት በቀለም ቅኔ የሚያስታውሱበት ቀን ነው ዛሬ፡፡
ፍቅሬ፡ ፍቅር አጀንዳ አይደለም፡፡ ውይይትን አይጠይቅም፡፡ መነጋጋርን አይጠይቅም፡፡ መስማማትን አይጠይቅም፡፡ የሰው ልጅ በልማድ በትር እየገረፈ ለጥያቄና መልስ ቢሰዋውም ፍቅር ጥያቄም መልስም አያስፈልገውም፤ ጠያቂም መላሽም አይሻም፡፡ ይህ ቀን ለተፋቀሩ ሁሉ ሳይሆን ለተጠያየቁና ለተመላለሱ ጥንዶች መታሰቢያነት ባክኗል፡፡ ቁርጥ ለሚበሉ ሳይሆን ለሚጎራረሱ ቀበጤዎች ሰለባ ሆኗል፡፡ ፍቅር መጎራረስን አይጠይቅም፤ አብሮ መሆንን አይጠይቅም፡፡ አብሮ መሆን ሰውን እንደ ንብረት የራስ ከማድረግ ስስት የሚመነጭ ነው፡፡ መተዋወቅ የፍቅር ህግ አይደለም፡፡
ፍቅሬ፡ ልኳንዳ ቤት የምትበይው ስጋ የየትኛው በሬ እንደሆነ ማወቅሽ ትርጉም የለውም፡፡ በሬውን ባታውቂኝም ስጋዬን እየበላሽ ነው፡፡ በፍቅርሽ ንክሻ እየማቀቅሁ ነው፡፡ ሳላውቅ የተኮስኩባቸውን ሰዎች ስጋ እየበላሁ እኔም ይሄው አለሁ፡፡ ይሄ ቀን “እወድሃለሁ-እወድሻለሁ” ተባብለው እጅ ለተመታቱ፤ ፍቅርን በመዳፍ መላተም ለማፅናት ለሚታትሩ እንጅ እንደኔና እንዳንች ሳንነጋገር ለምንበላላው ምስኪኖች አይደለም፡፡ ይህ ቀን እኛንም እንዲያስብ እሻለሁ፡፡ ለዛም ነው ይህን ቀይ ብሶት በቀይ ቀለም የከተብኩት፡፡ ለፍቅራችን ቀይ ስጋ መብያ ቢለዋ እንጅ ቀይ ወይን አያስፈልገንም፡፡ የኛ ፍቅር ሰካራም አይደለም፤ ከልማድ ወጥመድ አፈትልኳል፡፡ ሰላም ሁኝ የኔ አዳኝ!

Tuesday, January 31, 2012

የኛ ጉዳይ


1. ሰሞኑን በተሳተፍኩበት አንድ ውይይት ላይ ለአደንዛዥ ዕፅ ሱስ መስፋፋት ምክንያቱ የትውልዱ የሞራል ዝቅጠት ነው የሚል ሃሳብ ካንድ ምሁር ቀርቦ አሳፋሪ ክርክር አድርገንበታል፡፡ ሱሰኝነትን ከሞራል ዝቅጠት ጋር የሚያይዝ “ምሁር” በዚህ ዘመን ማግኘት ከባድ ነበር፤ አገሪቱ ብርቅዬ እንስሳትን ጨምሮ ብዙ ብርቅዬ ነገሮች ስላሉባት ግን ብዙ አልተደነኩም፡፡
2. ከወራት በፊት ራሱን ባጠፋው የኔሰው ገብሬ አሟሟት ዙሪያ በተለያዩ ፀሃፍትና ምሁራን የቀረቡ ሃሳቦችም ከፖለቲካ ብሶት በስተቀር የሚጨበጥ የሞራል ትንታኔ ማቅረብ አልቻሉም፡፡ ብዙዎች በየኔሰው ጤና ዙሪያ ከጥርጣሬ እንዳልፀዱ በቅርብ የገጠመኝ ሰው እማኜ ነው፡፡
3. ቀደም ብሎ በጁፒተር ሆቴል ተካሄዶ የነበረውን የHomosexuals ስብሰባን በተመለከተ የተለያዩ ፀሃፊዎች የፃፉት ጫጫታን እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ክርክር ለማድረግ አለመፍቀዳቸውን ታዝቤአለሁ፡፡
4. ሰሞኑን ደግሞ Tsegaye Hailesilassie በፌስቡክ ሰሌዳው ላይ በAtheists ላይ የሰነዘረውን ጉንተላ ተከትሎ የተደረጉት ክርክሮች በJudo-christian እይታ ተፅዕኖ ስር የወደቁና የፅንሰ-ሃሳብ ዕጥረት የሚታይባቸው ሆነው አግኝቻቼዋለሁ፡፡
ይህ ሲጠራቀም ኢትዮጵያውያን ምሁራንና ፀሃፍት ከፖለቲካ ባሻገር ትርጉም የሚሰጥ ሃሳብ ማመንጨት አይችሉም ወይ የሚል ብሶት ተናነቀኝ፡፡ ብሶቴን ተጋሩኝ!

Friday, January 27, 2012

አገሬ!


"…የግጦሽ ሳር ሲለመልም፤ ሲሰማሩ ሰደድ ሜዳ
አዝመራው ጣል ከንበል ሲል፤ ከብቱ ለሆራ ሲነዳ
ፈረስ ግልቢያ ስሸመጥጥ፤ ከወፎች ዜማ ስቀዳ
ልቤ በንፋስ ተንሳፎ፤ በዋሽንት ዋይታ ሲከዳ…
ያችን ነው ኢትዮጵያ የምላት
እመብርሃን ረሳሻት?"
__________________________________[ሎሬት ጸ.ገ.መ]
በአቡነ ጴጥሮስ ሰቆቃ ውስጥ ልጅነት ያተመው የትዝታ ዱካ ነፍስ ዘርቶ አቡኑን ሲያንሰቀስቃቸው እንሰማለን፡፡ አገር ማለት ምንድነው ለሚሉ የሎሬቱን ፍልስፍና በአቡኑ ትናጋ እንዲሰሙ እመክራለሁ፡፡ "ያችን ነው ኢትዮጵያ እምላት"፡፡ ሰው በልጅነቱ ይዞት ከሚወለደው ቡጫቂ ስጋ ይልቅ በህይወት ዘመኑ በምግብና በስራ የሚገነባው ይበልጣል፡፡ ይህ ራሳችን የገነባነውን ስጋ ራሳችን በቀላሉ ቆርጠን መጣል አንችልም፤ ህመሙ ስፍር የለሽ ነው፡፡ መንፈስም ከስጋ የተለዬ አይደለም፡፡ በሕይወት ውጣውረድ የተገነባ የአገር ፍቅርን ቆርጦ መጣል አይቻልም፡፡ ልምዱን ሌላ ቦታ ሌላ አገር ማዳበር ሊቻል ይችል ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ የልጅነት ስጋና መንፈስ የተገነቡት በዚች አገር ዳረንጎት ነው፡፡ ከአዳም ዕድሜ በኋላ የምናልፍበት የህይወት ቁልቁለት ሁሉ ለማንነት ብዙም እርባና የለውም፡፡ ሲግመንድ ፍሮይድ እንዳለው ልጅነት የማንነታችን መሰረት ነው፤ ካለዚህ መሰረት ማንነት ይሉት ጎጆ አይታሰብም፡፡
"…ያችን የልጅነት እናት
አዛኝቱ እንዴት ብለሽ ጥርሶችሽን ትነክሽባት?"

Thursday, January 26, 2012

አልታሰረችም


እውነት በፃፈ እጇ ላይ
ገመድ ተበተቡ አሉ
የሚፃፈው በአዕምሮ እንጅ
ከቶ በጣት እንዳልሆነ
የዘነጉ ቂሎች ሁሉ፡፡
  --------ለርዕዮት አለሙ እና መሰሎቿ