Tuesday, February 14, 2012

ለፍቅሬ (5) (የቫላንታይን ቀን መታሰቢያ)

ተኩስ ነው ፍቅር፡፡ እያንዳንዳችን የሰብዕናችንን ምላጭ እሳብን በየመንገዱ ሰው እንገድላለን፡፡ ምላጩን ስንስብ አይታወቀንም፡፡መገዳደል ብቻ፡፡ ‘በፍቅር ገደለኝ’ ይል የለ ሀበሻ ?! ሟች እንደታዳኝ አውሬ እየተንፈራፈረ ስጋውን ለአዳኝ ጥርስ ይገብራል፡፡ ምኞቱን ይገብራል፡፡ ህይወቱን ይገብራል፡፡
ፍቅሬ፡ ባህላችን ለቁርጥና ክትፎ ክብር አለው፤ ከኔ ወዲያ ቁርጥ! ይሄው ብይኝ!! ለቁርጥ የሚሆን ቀይ ስጋ በቀይ ልብስ አጊጠሸ ተመገቢ፡፡ ጥንዶች ሁሉ ለቀይ ስጋ መታሰቢያነት በቀይ ቀለም የሚያጌጡበት ቀን ነው ዛሬ፡፡ የሰው ልጅን በላኤ-ሰብነት በቀለም ቅኔ የሚያስታውሱበት ቀን ነው ዛሬ፡፡
ፍቅሬ፡ ፍቅር አጀንዳ አይደለም፡፡ ውይይትን አይጠይቅም፡፡ መነጋጋርን አይጠይቅም፡፡ መስማማትን አይጠይቅም፡፡ የሰው ልጅ በልማድ በትር እየገረፈ ለጥያቄና መልስ ቢሰዋውም ፍቅር ጥያቄም መልስም አያስፈልገውም፤ ጠያቂም መላሽም አይሻም፡፡ ይህ ቀን ለተፋቀሩ ሁሉ ሳይሆን ለተጠያየቁና ለተመላለሱ ጥንዶች መታሰቢያነት ባክኗል፡፡ ቁርጥ ለሚበሉ ሳይሆን ለሚጎራረሱ ቀበጤዎች ሰለባ ሆኗል፡፡ ፍቅር መጎራረስን አይጠይቅም፤ አብሮ መሆንን አይጠይቅም፡፡ አብሮ መሆን ሰውን እንደ ንብረት የራስ ከማድረግ ስስት የሚመነጭ ነው፡፡ መተዋወቅ የፍቅር ህግ አይደለም፡፡
ፍቅሬ፡ ልኳንዳ ቤት የምትበይው ስጋ የየትኛው በሬ እንደሆነ ማወቅሽ ትርጉም የለውም፡፡ በሬውን ባታውቂኝም ስጋዬን እየበላሽ ነው፡፡ በፍቅርሽ ንክሻ እየማቀቅሁ ነው፡፡ ሳላውቅ የተኮስኩባቸውን ሰዎች ስጋ እየበላሁ እኔም ይሄው አለሁ፡፡ ይሄ ቀን “እወድሃለሁ-እወድሻለሁ” ተባብለው እጅ ለተመታቱ፤ ፍቅርን በመዳፍ መላተም ለማፅናት ለሚታትሩ እንጅ እንደኔና እንዳንች ሳንነጋገር ለምንበላላው ምስኪኖች አይደለም፡፡ ይህ ቀን እኛንም እንዲያስብ እሻለሁ፡፡ ለዛም ነው ይህን ቀይ ብሶት በቀይ ቀለም የከተብኩት፡፡ ለፍቅራችን ቀይ ስጋ መብያ ቢለዋ እንጅ ቀይ ወይን አያስፈልገንም፡፡ የኛ ፍቅር ሰካራም አይደለም፤ ከልማድ ወጥመድ አፈትልኳል፡፡ ሰላም ሁኝ የኔ አዳኝ!