Monday, May 4, 2015

የግንቦት ወሬ /ክፍል አንድ/



የግንቦት ወሬ /ክፍል አንድ/

(ውብሸት ታደለ)

ግንቦት እየመጣ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ግንቦት የዝንብ እና የንብ ወቅት ነው፡፡ ዝንቡ በራሱ ስልጣን፣ ንቡ በገዢዎቻችን ትዕዛዝ አካባቢያችንን ይቆጣጠራሉ፡፡ ከቤታችን በር ላይ ከቆመ የመብራት ግንድ ላይ የንቢቱ ስዕል ተለጥፏል፡፡ ይህን ስዕል የሳለው ሰው እንደ አንዳንድ ሰዓሊዎች ድብቅ መልዕክት ማስተላለፍ የፈለገ ይመስለኛል፡፡ የንቢቱ ቅልጥም የMHDን¹፣ ውፍረቷ ደግሞ የአባዱላን ሰውነት የሚወክል ሲሆን ይህም የድርጅቱን የአበላል ታሪክ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ የገበሬው ንብ ከሲታና ለስዕል እንኳን የማትበቃ ስትሆን የድርጅቱ ንብ ግን 24 ዓመት በደንብ የተቀለበች የሀረር ሰንጋ ነች፡፡ ለመሆኑ ንቢቱ እንዲህ የደለበችው አበባ ከዬት አግኝታ ነው? ገዢዎቻችን ንቢቱ አበባውን ያገኘችው ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ እንደሆነና አፍቃሪዋም ገበሬው እንደሆነ ቢናገሩም ህዝቡ ግን ንቢቱ የደለበችው ስኳር እየላሰች² ነው ይላል፡፡ የሆነው ሆኖ ኢህአዴግ ከዝንብ ጋር በግንቦት የመጣ ድርጅት በመሆኑ ዝንብን ምልክት ቢያደርግ የበለጠ ምክንያታዊ ይሆን ነበር፡፡ በዚያ ላይ ለቆሻሻ ግብሩ ዝንብ እንጅ ንብ አትመጥነውም፡፡ ለንቢቱ ማማለያ አበባን ምልክታቸው ያደረጉ ፓርቲዎችም ዝንቢቱን ለመግደያ ጭራን ምልክታቸው ያደርጉ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ቅንጅት በ1997 ምርጫ ሁለት ጣትን ምልክት ካደረገ በኋላ የተለያዩ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክታቸውን በተለያዩ ጣቶች ዙሪያ ወስነዋል፡፡ የቀረው ብቸኛ ጣት የመሃል ጣት ሲሆን እርሱንም ለብልግና ቅርብ የሆኑ ወጣቶች ለቀጣይ ምርጫ ምልክት እንደሚያደርጉት ዝተዋል፡፡

በግልፅ ለመነጋገር፣ ኢህአዴግን ከንብ ጋር የሚያገናኙት ብቸኛ ነገሮች የመናደፍ ልማዱና ለስካር (ለጠጅ/ለቢራ) ቅርብ መሆኑ ነው፡፡ የነቁትን በዱላ፣ ያልነቁትን በቢራ እየዘረረ አገሪቱን እየገዛ ነው፡፡ በዳሽን ከፍታ ላይ የትውልድ ስካር ታውጇል፡፡ በቃሊቲ ሸለቆ ውስጥ የትውልድ እንባ ተቁሯል፡፡ የጊዜው ዘፈን “ኧረ ንቦ አትናደፊ” ቢሆንም ንቢቱ ግን ከመናደፍ አልቦዘነችም፡፡ እንደውሻ ንብ መርዟን እንጅ ማሯን ቀምሰነው አናውቅም፡፡ ከአበቦች ቀስም ይልቅ የእኛ እምባ ይጣፍጣታል፡፡ ፃድቁ አቡዬ ለፅድቅ ሲሉ እምባቸውን ለወፍ እንዳጠጡት እኛም ለመሰንበት ስንል እምባችንን ለንቢቱ እያጠጣን ነው፡፡ የኢትዮጵያ እናቶች ጡታቸውንም ዓይናቸውንም እያጠቡ ነው፡፡
   
ያም ሆነ ይህ ግንቦት የበራሪ ነፍሳት እና የፖለቲካ ወር ነው፡፡ ከግንቦት ልደታ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ህዝብ በሰፊው የሚታወቁ ቀናት ግንቦት ሰባት እና ግንቦት ሃያ ናቸው፡፡ በግንቦት ልደታ የሚጀመረው የልደት ንፍሮ ክረምቱን ሙሉ በሚዘልቅ የሞት ንፍሮ ይታጀባል፡፡ አደባባዩ በህዝብና በጥይት ጩኸት ይሞላል፤ ጌቶቹም ይህን ልዩ የሙዚቃ ስልት እያዳመጡ የሙዚቃው አቀናባሪ የጥይቱን ድምፅ ከፍ እንዲያደርገው ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡ በእነበረከት አስተሳሰብ ጠብመንጃ የሙዚቃ እንጅ የጦር መሳሪያ አይደለም፡፡ ሰልፈኛውን ለመበተን ፌዴራል ፖሊስ ለምን አስለቃሽ ጭስ አይጠቀምም የሚል የዋህ ጥያቄ ሰዎች ሲያነሱ እሰማለሁ፡፡ መልሱ ግልፅ ነው፤ ሰልፈኛው ቀድሞውኑ እያለቀሰ ነው የሚኖረው፤ እያለቀሰ ነው የሚሰለፈው፡፡ በዚህ ሁሉ መሃል ገዢዎቻችን ጥቁር ሳቃቸውን ይስቃሉ፡፡ ከንቧ ይልቅ ለቀፎዋ ቅርብ የሆነውን አስተሳሰባቸውን ይዘው በዚህ ዘመን ህዝብን በዱላ መግዛት ይፈልጋሉ፡፡ አገር በሚያገማ የዘር ፖለቲካ ታውረው፣ ድንቁርናን እንደርዕዮተ-ዓለም ተቀብለው፣ አገሪቱን እንደዶሮ ስጋ ቆረጣጥመው በሏት፡፡ በነገራችን ላይ፣ ንብ ብሄሯ ምንድነው?

ኢህአዴግአውያንን በዚህ ሰዓት ከሚያስጨንቋቸው ነገሮች ዋናው የቀለም አብዮት ነው፡፡ የዘመኑ ሴቶች ስማቸውን እንደሚቀይሩት ዓይነት የስም ለውጥ ያደረገው በግብር ግን ያልተቀዬረው ኢቲቪ በጉዳዩ ላይ መቀባጠር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ የቀለም አብዮትን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የፖለቲካ ተንታኞች ከፖለቲካ ሳይንስ ይልቅ ለቀለም ቅብ ወይም ለስዕል ጥበብ ቅርብ የሆኑ ይመስለኛል፤ ከአብዮቱ ይልቅ ቀለሙ ላይ ቢያተኩሩ መልካም ነው፡፡ በብሄራዊ ደህንነት ስም ዜጎችን ማረድና ማዋረድ አዲስ የጭቆና ስልት አይደለም፤ ደርጎቹም በትዝታ የሚያወጉን ያንኑ ነው፡፡ የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ህዝብን መግደልና ማሰቃዬት ምን ዓይነት የደህንነት ፍልስፍና ነው?! 

ግንቦት እየመጣ ነው …

ግንቦት ሃያ እየመጣ ነው …

ከዚያ በፊት ደግሞ ግንቦት ሰባት እየመጣ ነው፡፡

ህዝቡ ግን “ግንቦት ሰባት… ግንቦት ሰባት” ሲል የሚውለው የምርጫው ቀን መቀዬሩን አልሰማም እንዴ? ወይስ ህዝቡ ራሱን ማሸበር ጀመረ? ይህን ጉዳይ ማጣራት የገራፊዎቻችን ድርሻ ነው፡፡ የአብዮቱ ስም ቢጫ እንዲሆን የጠቆምከው ወዳጄ! ምክንያትህን ለማጠናከር ከውሃ ጀሪካን ሰልፍ ባሻገር የዘይት ጀሪካን ሰልፍ ተጀምሮልሃልና ደስ ይበልህ፡፡ አብዮቱም የሚነሳው ለዘይት ሰልፍ በወጣው ህዝብ እንደሚሆን አትጠራጠር፡፡ 

ግንቦት የሙቀት ወር ነው፡፡ አየሩም ፖለቲካውም ይሞቃል፡፡

ግንቦት የማጉረምረም ወር ነው፡፡ ሰማዩም ህዝቡም ያጉረመርማል፡፡

የምወራረድበትን እውነት ግን ልናገር- አብዮቱ በፍፁም አይቀርም፡፡ ምክንያቱም፣ ኢቫን ፓቭሎቭ³ እንደፃፈው there’s something called Freedom Reflex! ነፃነትን መሻት ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ተፈጥሯዊው እውነት ኢትዮጵያዊም እውነት የማይሆነው ደግሞ ኢትዮጵያውያን ሰው ሰራሽ ከሆኑ ብቻ ነው፡፡ “We Need Freedom. Freedom! Freedom! Freedom!!!”

(ይቀጥላል)

¹ Mengistu Hailemariam Dessalegn (ዘላለም ክብረት ከእስር ቤት በፃፈው ደብዳቤ ላይ ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም ደሳለኝን ለመጥራት የተጠቀመበት ቃል)
² የቀድሞው (የአሁኑም) ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የድሮ ጓዳቸው ሙስና እንደበላ ለመግለጽ የተጠቀሙበት ቃል
³ ከዲዮጋን ቀጥሎ በውሻው ዝነኛ የሆነ ሊቅ፤ ከራሱም በላይ ውሻው ዝናኛ የሆነ፡፡ “የፓቭሎቭ ውሻ” ሲባል አልሰማችሁም?!

No comments:

Post a Comment