Saturday, May 9, 2015

የግንቦት ወሬ (ክፍል ሁለት)



የግንቦት ወሬ (ክፍል ሁለት)
(ውብሸት ታደለ)
የዘንድሮው ምርጫ ለቀልድ አዋቂ ሰው በሳቅ የሚገድል ጨዋታ ነው፡፡ እንደኔ ዓይነቱ ቀልድ የማያውቅ ጅላጅል ግን ኢህአዴግን እንደፓርቲ ቆጥሮ በኢህአዴግ ድርጊት ሲቃጠል ይውላል፡፡ መቼም ኢህአዴግ ፖለቲካን የሚመለከተው በልጅነታችን እንደምንሰራቸው የመንደር ተንኮሎች ነው፡፡ ተንኮል መስራት ያልበሰሉ ጭንቅላቶች ሙያ እንደሆነ ለማወቅ ከልጅነታችን በላይ ምስክር የለም፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች በሚሰሩት የልጅ ተንኮል ከመሳቅ ይልቅ የምበሳጨው ለምንድነው? ኢህአዴግ ማለት 24 ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያን ሲገዛ የመሪዎቹ ዓላማ በግልፅ የማይታወቅ ድርጅት መሆኑ ጠፍቶኝ ነው? ቀድሞውኑ አገሬን አጥንት እንዳዬ ጉንዳን ሊቀራመቷት መነሳታቸው ጠፍቶኝ ነው ወይ? ለምንድነው በቀልዳቸው የማልዝናናው? በአገር መቀለድ ብርቅ ነው እንዴ? እንደነዚህ ዓይነት ጥያቄዎች አዕምሮዬን ቢሞሉትም በቀልዳቸው ግን አልስቅም፡፡ ለምን?...

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለስልጣን ሲሉ የስልጣን ተቀናቃኝን ማሰርና መግደል በየገፁ የምናነበው ሃቅ ነው፡፡ ስልጣንን ለማስጠበቅ ሲባል ልጆችን ለተቀናቃኝ ወገን ከመዳር ጀምሮ ተቀናቃኝን እስከማሰር ብሎም እስከመግደል የሚደርሱ እርምጃዎች እንደነበሩ አንብበናል፡፡ ይህ እውነት ለአውሮጳ ታሪኳ ለአፍሪቃ ደግሞ ዜናዋ ነው፡፡ ነገር ግን አፍሪቃ አዳዲስ ዜናዎችን ማሰማት ጀምራለች፤ ወደናይጀሪያ በኩል የሰማነው አዲስ ዜናም የዚሁ አካል ነው፡፡ እኛ ግን ግንቦት 20 ላይ እንደቆምን ነን፡፡ አሁንም ስልጣን በጠመንጃ እንጅ በሰለጠነ ፖለቲካ የማይገኝ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የምርጫ ኮረጆ የወያኔዎቹ ጥይት ማዘያ ከረጢት ሆኗል፡፡ ይህን የጅል ጨዋታ የማወራው ድሮውንስ እነጅቦን ስለማላውቃቸው ነው? ድሮስ ቢሆን የ2007 ኢትዮጵያ ወደ 1997 ኢትዮጵያ ታድጋለች ብዬ ነው? ወይስ እነጅቦ ሃብታቸውን አሽሽተው ጨርሰዋል ብዬ ነው? ይህ ሁሉ ባይጠፋኝም በቀልዳቸው ግን አልስቅም፡፡ ለምን?...

ኢህአዴግ ሰዎችን ማሰር የእጅ ሰዓት እንደማሰር የሚቀለው ድርጅት ቢሆንም ለአቅመ እስር የበቁ ነቄ ልጆች ግን አሁንም በየመንደሩ አሉ፡፡ ብርቱካንን ሲያስር ርዕዮት፣ ርዕዮትን ሲያስር ማህሌት፣ ማህሌትን ሲያስር ወይንእሸት፣ ወይንእሸትን ሲያስር…፡፡ ኢትዮጵያ ነቄ ልጆች ቢያንሷትም አላጣችም፡፡ በ(ዣን)ጥላ ስር የተሰባሰቡ ልጆች ሰማያዊ ቀለም ተቀብተው መጥተዋል፡፡ እነጅቦም ጥላ ይዞ የሚራመድ ሰው ባዩ ቁጥር የሚገቡበት ይጠፋቸዋል፡፡ እንዲያውም ፀረ-ጥላ መሆናቸውን ተከትሎ “ጥላ-ቢስ” የሚል መጠሪያ ወጥቶላቸዋል አሉ፡፡ በየመንደሩ ወሬ ሲቃርሙ የሚውሉ ካድሬዎችን ለመግለፅ “ጥላ-ቢስ” ከሚል ቃል በላይ የት ይገኛል?! በነገራችን ላይ ህግ ማውጣት የሚወዱት ሟቹ ጠቅላያችን በህይወት ቢኖሩ ኖሮ ጥላ መያዝንና ሰማያዊ ቀለም መጠቀምን በህግ ይከለክሉት ነበር፡፡ በፓርላማው ተገኝተውም ህጉ እንከን የማይወጣለትና በውጭጭ የተኮረጀ መሆኑን ይናገሩ ነበር፡፡ አንቀፆቹን ልገምት…

ጥላ ወዳዱ የአገው ህዝብ ከአሁን በኋላ በጥላ ምትክ ዱላ እንዲይዝ…

ዓይነ-ጥላ፣ ጆሮ-ጥላ፣ ጥላሸት፣ ወንድም ጥላ፣ ጥላ-ቢስ፣ ወዘተ. የተሰኙ ቃላትን የተጠቀመና ለመጠቀም ምክንያት የሆነ፤ ከተጠቀመው ሰው ጋር አብሮ የነበረ አዋጁን እንደጣሰ ይቆጠራል…

“ጥላ ቆርቆሮ ፋብሪካ” ድርጅቱን በጥላ ስም የሰየመ በመሆኑ በጥላ አራማጅነት ተፈርጇል፡፡ በመሆኑም “ጥላ ቆርቆሮ”ን የገዛ፣ የሸጠ፣ ያሻሻጠ፣ ሲሸጥ ያየ፣ ወዘተ. አዋጁን እንደጣሰ ይቆጠራል…

ሰማያዊ ቀለም የተቀቡ ቤቶች፣ “በሰማያት የምትኖር” የሚለው የፀሎት ቃል፣ “የሰማዩ አሞራ” በሚል የሚጀምረው ግጥም፣ ወዘተ. ላይ ማስተካከያ ሳይደረግባቸው ጥቅም ላይ ያዋላቸው ሰው አዋጁን እንደጣሰ ይቆጠራል…

ሟቹ በህይወት ቢኖሩና ይህ ህግ ቢወጣ ኖሮ እስቅ ነበር? ጅቦቹ የሚያመጡት ጨዋታ ሁሉ የማያስቀኝ አስቂኝ ስላልሆነ ነውን? ወይስ በአገር ላይ ሲቀለድ ስቄ አላውቅም? ያም ሆነ ይህ በቀልዳቸው አልስቅም፡፡ ለምን?...

ምክንያቱም…

ቀናትን በሳቅ ማለፍ የሚቻለው ነገ ሌላ ቀን እንደሚሆን ሲታሰብ ነው፡፡ ጭቆና ግን ዛሬህን ብቻ ገድሎ የሚያቆም ነገር አይደለም፡፡ ጦሱ ጊዜን ተሻጋሪ ነው፡፡ የደርግ ግፍ የጎዳት የያኔዋን ኢትዮጵያን ብቻ አይደለም፡፡ ደርግ የዚያን ትውልድ ህይወትና የዚህን ትውልድ ወኔ ገድሎ ነው ያለፈው፡፡ ዛሬ ጅቦቹ የሚዘሩት ግፍስ ነገ ምን ሆኖ ይበቅላል ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በዘርና በሆድ ላይ የተዘራ ፖለቲካ ፍሬው ምን ይሆናል ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ የሚያሳስበኝ የጅቦቹ አለመሄድ ሳይሆን በጊዜ አለመሄዳቸው ነው፡፡ በእያንዳንዱ ቀን የሚሰሩት ግፍ ሲሰላ ለጥቂት ጊዜ በዚሁ ከቀጠሉ ከዚያ በኋላ ሄዱም አልሄዱም ትርጉም አልባ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እንደአገር ለመቀጠል የሚያስችለን ሰንሰለት ይበጠሳል፡፡ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” የሚባለው ያኔ ነው፡፡ ጅቦቹ ከሄዱ በኋላ መጮህ ነገን አይታደግም፡፡ 

አሁን ጊዜው የጩኸት ነው፤ የለቅሶ ነው፡፡ ፈፅሞ የሳቅ ጊዜ አይደለም፡፡ ዛሬያችንን ገድለውታል፤ ነገአችንን እንዳይደግሙት እንጩህ፡፡…

ከግንቦት ሰማይ ጋር አብረን እናጉረምርም፡፡

(ይቀጥላል)

No comments:

Post a Comment