Wednesday, October 21, 2015

የኦሮሞ ትርክቶች (Oromo Narratives)



የኦሮሞ ትርክቶች (Oromo Narratives)

ኢትዮጵያንና ህዝቧን በጥልቀት ያጠኑት ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን በኦሮሞ ጥናት ማህበር ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ባቀረቡት አንድ ፅሁፍ የኦሮሞ ልሂቃንን በተመለከተ ሶስት ዓይነት ትርክቶች (Narratives) እንዳሉ ገልፀው ነበር፡፡ እነሱም ባህላዊው ትርክት፣ የቅኝ ግዛት ትርክትና የኢትዮያዊነት ትርክት ናቸው፡፡ እስኪ በራሳችን መንገድ ትርክቶቹን እንቃኛቸው፡፡ 

ባህላዊው ትርክት (Traditional Narrative) የኦሮሞን ባህልና ማንነት በተመለከተ የሚቆረቆርና በአመዛኙ የኦሮሞ ባህላዊ የዴሞክራሲ ስርዓት በሆነው በገዳ ስርዓት ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ በእኔ የንባብ ልምድ ይህን ስርዓት በተመለከተ እስከጥግ የፃፉ ሰው ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ ናቸው፡፡ ለአውሮጳም ሆነ ለኢትዮጵያ ስርዓት እንግዳ የሆነው የገዳ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዴት በአውሮጳውያን ፀሃፍት አድልኦ እንደተደረገበት በመተንተን በዴሞክራሲ ቀዳሚነቱን ያስረዳሉ፡፡

የቅኝ ግዛት ትርክት (Colonialist Narrative) ኦሮሞዎች በታሪክ ውስጥ እንደተበደሉና እንደተሰቃዩ የሚያትትና በምሬትና እምባ ላይ የሚያጠነጥን ትርክት (Lachrymose Narrative) ነው፡፡ በዚህ ትርክት ውስጥ የሚኒሊክ የግዛት ማስፋፋት ጉዳይ ሰፊ ቦታ አለው፡፡ በዚህ የሚኒሊክ ግዛት ማስፋፋት ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥኑ ዕይታዎችን ፕሮፌሰር መረራ በሶስት ይከፍሏቸዋል፡- የጭቆና፣ የአገር ግናባታ እና የቅኝ ግዛት ብለው፡፡ ጉዳዩን ከብሄራዊ ጭቆና ጋር የሚያያይዙት ወገኖች በአንድ በኩል፣ የአገር ግንባታ ሂደት አካል መሆኑን የሚናገሩት በሌላ በኩል፣ እና ኦሮሚያ በኢትዮጵያውያን ቅኝ ተገዝታለች የሚሉት በጫፍ በኩል ሆነው ክርክሩን ያጦፉታል፡፡ ፕሮፌሰር መረራ ጉዳዩን በቅኝ ግዛት የሚመለከቱትን እነኦነግን ሲወርፉ በሻዕቢያ የትግል ስልት የተማረኩ እንጅ የኦሮሞን ማንነት የሚያውቁ አይደሉም በማለት ነው፡፡ የኦሮሞንም ታሪክ ከጨቋኞችም ከተጨቋኞችም ውስጥ እንደሚካተት ያስረዳሉ፡፡ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ በበኩላቸው ጉዳዩ ጥንታዊ የግዛት ማስፋፋት ዓይነት እንጅ የቅኝ-ግዛት ጉዳይ እንዳልሆነ በመተንተን ይህን ዕይታ በዩሮ-ሴንትሪዝም (Euro-centrism) ይከሱታል፡፡ ያም አለ ይህ በዚህ ትርክት ዙሪያ የሚገኙ ልሂቃን በኦሮሞ መሬትና ኃብት ላይ የሚያተኩሩ፣ ለአፋን ኦሮሞ ዕድገትና ኦሮሞዎች በኢተዮጵያ ለሚኖራቸው ፖለቲካዊ ውክልና የሚጨነቁ ናቸው፡፡

ሶስተኛው ትርክት (Ethiopianist Narrative) የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተጫወተውን ሚናና ከሌሎች ህዝቦች ጋር እንደ ድርና ማግ እንደተሳሰረና የኢትዮጵያን ማህበረሰብ እንደፈጠር የሚገልፅ ነው፡፡ ይህ ትርክት ኦሮሞዎች ስለራሳቸው ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያስተካክሉ የሚወተውት ነው፡፡ በዚህ ትርክት ውስጥ ብዙ ታሪካዊ ሂደቶች ይገለፃሉ፡፡ ሱስንዮስ፣ ባካፋ፣ ኢያሱ 2ኛ፣ ኢዮአስ፣ አሊ፣ ጉግሳ፣ ልጅ እያሱ፣ ወዘተ. በትርክቱ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚደመጡ ናቸው፡፡ አፄ ባካፋ ኦሮምኛ ይናገር እንደነበር፣ ኦሮምኛ የቤተ-መንግስት ቋንቋ ሆኖ እንደነበር፣ ኢያሱ 2ኛ ኦሮሞዋን ውቢትን እንዳገባ፣ የጁ ኦሮሞ ለረጅም ጊዜ ኢትዮጵያን እንዳስተዳደረ፣ ኦሮሞዎች በዘመናዊት ኢትዮጵያ ምስረታና አስተዳደር ውስጥ የነበራቸው ሚና፣ ወዘተ. ተደጋግሞ ይገለፃል፡፡ በሁሉም አቅጣጫ ከተለያዩ የአገሪቱ ህዝቦች ጋር ተዋህደውና ተሳስረው መኖራቸውን ያስገነዝባል፡፡ ይህን ትርክት ጠቅለል ባለ መልኩ ከጥንቱ ታሪካችን ጀምሮ ለመነካካት የሞከረው ባለፈው ክረምት የታተመው የታቦር ዋሚ “የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች” የተሰኘ መፅሃፍ ነው፡፡ መፅሃፉ በውገና ከሚከሳቸው ሰዎች በባሰ መልኩ ራሱ የውገና ድርሰት በመሆኑ የኢትዮጵያን ታሪክ በጥቂቱም ለማንበብ ያልሞከራችሁ ሰዎች ባታነቡት (ብታቆዩት) ይመከራል፡፡ ይህን ሶስተኛውን ትርክት ለመግለፅ ግን መፅሃፉን መጥቀስ ቀላል ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

ሶስቱ ትርክቶች የአሁኖቹን አክቲቪስቶች ይገልጧቸዋል? ከገለጧቸውስ የትኛው ላይ ሊካተቱ ይችላሉ?

እንግዲህ ሶስቱ የትርክት ክፍሎች የተለዩት በሶሲዮሎጂስቶች ቋንቋ እንደሃሳባዊ ጎራዎች (Ideal Types*) ነውና አንድ ሰው ከሶስቶቹ ውስጥ በአንዱ ወይም በሁለቱ አልያም በሁሉም ትርክቶች ውስጥ ሊገኝ ይችላል፡፡

በእኔ እይታ የሶሻል ሜዲያውን የከበቡት ዋናዎቹ አክቲቪስቶች ከሶስተኛው ትርክት (Ethiopian Narrative) ላይ ቆመው የብሶት ትርክቱን (Lachrymose Narrative) የሚያራምዱ ናቸው፡፡ እየገነቡ ነው ሲባል እያፈረሱ የሚገኙ ናቸው፡፡ ምናልባት ሌላ ትርክት የሚፈጠርበት የሽግግር ጊዜ ይሆናል፡፡ ወይም አዲሱን ምድብ ለመሳል ከብዶኝ ይሆናል፡፡ ለዚያ ይሆናል ነገራቸው የማይገባኝ፡፡ ይህን አዲሱን የአክቲቪስቶች መፍጨርጨር “የጃዋርያን ትርክት” (Jawarian Narrative) እንበለው ይሆን? ፡) “ከኦሮሞ ፖለቲካ ወደ ጃዋር ፖለቲካ” ያለው ማን ነበር?! 

ለማንኛውም ግን ኢትዮጵያ ትቅደም!

*Ideal Types= በተደጋጋሚ የሚስተዋሉ ባህርያትን በመውሰድ ለንፅፅርና ለትንተና ያመች ዘንድ የምንፈጥራቸው ሃሳባዊ ጎራዎች ናቸው፡፡ የዚህ ዘዴ ፈጣሪ ሌላ ይሁን እንጅ ታዋቂው ሶሲዮሎጂስት ማክስ ቬበር ዋነኛ አቀንቃኝ ነው፡፡    
 

No comments:

Post a Comment