Sunday, May 10, 2015

የግንቦት ወሬ (ክፍል ሶስት)



                   የግንቦት ወሬ (ክፍል ሶስት)
(ውብሸት ታደለ)

የደርግ ሰዎች ያን ትውልድ እስኪደክማቸው ድረስ ገርፈውትና ገድለውት ሲያበቁ ከስልጣን ወረዱ፡፡ ያንን ያደረጉት ለአገሪቱ ደህንነት እንደሆነ እያወሩ ነው፡፡ ደግነቱ የሚሰማቸው የለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሰማቸው የሚያስገድዱበት ጊዜ አልፏልና፡፡

አሁን ደግሞ የወያኔ ሰዎች በተራቸው ሰው ሲገርፉና ሲገድሉ ይውላሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት ለአገሪቱ ደህንነት እንደሆነ ያወራሉ፡፡ ቀን እስኪያልፍ ድረስ እያስገደዱ ወሬያቸውን ይግቱናል፡፡
አገሪቱም ለደህንነቷ የልጆቿን ደም የምትጠባ ቆሌ ሆናለች፡፡ የኢትዮጵያ ጤና የሚጠበቀው የልጆቿን ደምና እምባ ስትጠጣ ሆኗል፡፡ አገሪቱ የምትከበረው ልጆቿን ስታዋርድ፣ የምትለብሰው ልጆቿን ስታራቁት፣ ዳግም የምትወለደው ዳግም ልጆቿን ስትቀብር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዳሴ የሚፀናው በልጆቿ የግርፋት ሰምበር ነው፡፡ እነበፍቃዱ፣ እነማህሌት፣ እነአቤል፣ እነአብርሃ፣ እነተመስገን…ሲገረፉ ካላዬች ኢትዮጵያ ደህንነት አይኖራትም፡፡ ለኢትዮጵያ ደህንነት ኢትዮጵያውያን መገረፍ፣ መሰደድ፣ መዋረድ፣ መገደል አለባቸው፡፡ ይህ የጌቶቻችን የደህንነት ፍልስፍና ነው፡፡
ደርጎቹ አገር የሚመስላቸው መሬት ብቻ ነው፡፡ ለመሬቱ ደህንነት ህዝቡን እንግደለው ብለው ህዝቡን ገደሉ፡፡

የአሁኖቹ ደርጎች ግን “አገር ማለት ሰው ነው” ብለው ዘመሩ፤ እናም መሬቱን ሸጡ፡፡ መሬታችንን ሽጠው አወዳይና በለጨ ቃሙበት፡፡ በቢራና በውስኪ ሰከሩበት፡፡ ስካር ባሰረው አንደበት “አገር ማለት ሰው ነው” እያሉ በውድቅት ሌሊት ሲዘምሩ ሰማን፡፡

የቢራው ስካር ሲያበቃ ደግሞ በደም መስከር አማራቸው፡፡ እናም ለአገር ሲሉ የህዝቡን ደም አፈሰሱ፡፡ ለኦሮሚያ ልማት ሲሉ ኦሮሞዎችን ገደሉ፡፡ ጋምቤላ ትለማ ዘንድ የጋምቤላ ልጆች ማቀቁ፡፡ ለኢትዮጵያ ልማት ሲሉ ኢትዮጵያውያንን አዋረዱ፡፡ 

እናም መሬቱንም ሰውንም ናቁ፡፡ አገር ማለት ምንድነው? አዲሱ መዝሙር ገና አልወጣም፡፡…

የወያኔ ሰዎች በብዙ መልኩ ዕድለኞች ናቸው፤ ዕድላቸውን አልተጠቀሙበትም እንጅ፡፡ ትዕቢት የት ላይ እንደሚጥል ከደርግ የመማር ዕድል ነበራቸው፤ አላቸውም፡፡ ከህዝባቸው ጋር በቀላሉ መገናኘትና መደማመጥ የሚችሉበት የቴክኖሎጂ ዘመን ላይ ነው የመጡት፡፡ ጭቆናን የሚታገስ ጫንቃ ያለው ህዝብ አላቸው፡፡ ይህን ዕድላቸውን ግን ሊጠቀሙበት አልፈቀዱም፡፡ ነገ እንዳይታዘንላቸው እየሆኑ ነው፡፡ ግፋቸው ግድቡን ሞልቶ እየፈሰሰ ነው፡፡ ግፍ የሚፈጥረው ኃይል ደግሞ በሜጋ ዋት የሚለካ አይደለም፡፡ ዕልቆ-ቢስ ነው፡፡

በየትኛውም ቋንቋ ቢገለፅ የማይደበዝዝ አንድ እውነት አለ፡፡ ነፃነትን ፍለጋ የወጡ ልቦች ሳያገኟት አይመለሱም፡፡ ወይ በጉዞ ላይ እንዳሉ ነፃ ይወጣሉ፤ ወይም ጉዞው ነፃ ያወጣቸዋል፡፡ ይህን ሃቅ ረስታችሁት ከሆነ የበርሃ ማስታዎሻችሁን አገላብጡት፡፡ አለበለዚያ ግን አገር እየገደላችሁ መዝሙር አትቀያይሩ፡፡ አገር ማለት አገር ነው፤ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ኢትዮጵያን በብልቶቿ አትጥሯት፡፡ መሬት፣ ሰው፣ ታሪክ፣…ብልቶቿ እንጅ ሁነቶቿ አይደሉም፡፡

እባካችሁ ጭካኔው ይብቃችሁ፡፡ እምባ ማዬት ባያሳዝናችሁ እንኳን እንዴት አይሰለቻችሁም?!

ጊዜው እየመጣ ነው፡፡ ከግንቦት ደመና ጋር የሚያጉረመርመው ድምፃችን ሳይዘንብ በፊት ከራሳችሁ ጋር ተማከሩ፡፡ የልጆቿን ደም የምትጠባና ልጆቿን እንደፍየል ወጠጤ የምትቆጥር አገር አንፈልግም፡፡ ልጆቿን የምታዋርድ አገር አንፈልግም፡፡ 

ጅቦች ሆይ አገራችንን መልሱልን!!


No comments:

Post a Comment