Wednesday, May 13, 2015

አቦይ ስብሃትን እንደሰማኋቸው



አቦይ ስብሃትን እንደሰማኋቸው



(ውብሸት ታደለ)


በአጋጣሚ በመንደራችን መብራት ስለመጣ ቴሌቪዥን የማዬት ዕድል አገኘሁ፡፡ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አዲሱ ገ/መድህንና ሌሎች ሰዎች የመሩት ስብሰባ እየተላለፈ ነበር፡፡ ፈገግ ካሰኙኝ ንግግሮች መካከል የኢህአዴግ ፓርቲን በመወከል የቀረቡት አቶ ዘሪሁን ተሾመ (ከተሳሳትኩ አርሙኝ ፡) ) ያቀረቡት የሆድ-አደር ዘይቤን የተከተለ ንግግር አንዱ ነው፡፡ ይህን ስብሰባ ለመናቅ የዚህ ሰውዬ መገኘት ራሱ በቂ ነው፡፡ የመድረኩ ፀሃፊ አቶ ገብሩ ደግሞ የምራቸውን በብሶት እየተናገሩ ነበር፡፡ የአቶ ገብሩን ጥያቄዎች ለመመለስ አፋቸውን የከፈቱ ብዙዎች ቢሆኑም ጥያቄያቸውን ለመረዳት አዕምሯቸውን የከፈቱ ግን አልነበሩም፡፡ የአቶ አየለ ጫሚሶ የመንፈስ ወንድም አቶ ትዕግስቱ አወል ደግሞ ሌላው ኢህአዴግን በመወከል ክርክር ያደረገ ሰው ነበር፡፡ የፓርላማ ወንበር እንደጫት ቤት ወንበር “አብሽር” በመባባል የሚገኝ መስሎት ኢህአዴግን “አብሽር” ሲል አምሽቷል፡፡ ጥርስ ሳይኖረው እንዲህ ሆድ ያዘዘበት ጥርስ ቢኖረው ምን ሊያደርገን ኖሯል?! ፡)

በዚህ ሁሉ ድራማ መጨረሻ አካባቢ አቦይ ስብሃት የተናገሩት ነገር ልቤን ነክቶኛል፡፡ አቦይ እንዳሉት ተለይቶ የተጨቆነ ብሔር የለም… ሁሉም ብሄር ነው የተጨቆነው… ለድንጋይ መወራወር የሚያበቃ ነገር የለም፡፡ አቦይን በተሳሳተ መንገድ ተረድቻቸው ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ብሄር እየተጨቆነ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ግን ጭቆናው ድንጋይ እስከመወራወር አያደርስም ባይ ናቸው፡፡ ምን ዓይነት ጭቆና ነው ድንጋይ እስከመወራወር የሚያደርሰው? 

አቦይ በንግግራቸው ውስጥ የህዝቡን ብሶትና ቁጣ የተረዱ ይመስላል፡፡ የአብዮት ስጋት አለባቸው፤ ፍርሃት ይነበብባቸዋል፡፡ ኢቢሲም በየቀኑ የሚያንፀባርቀው ይህንን ስጋትና ፍርሃት ነው፡፡ የፖለቲካ ችግሮቻችን ሁሉ መነሻም ስጋትና ፍርሃት ናቸው፡፡ በስጋትና ፍርሃት ላይ ተመስርተው የሚወሰዱ የዘፈቀደ እርምጃዎችና ግፎች ሌላ ስጋትና ፍርሃት ይፈጥራሉ፡፡ ይህ ሂደት ሲደጋገም እውነተኛው አስፈሪ ጊዜ ይመጣል፡፡

አጋጣሚ ሆኖ በመንግስት ተቋም ውስጥ ባለሙያ ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ ቢያንስ የመንግስትን አሰራርና ፍላጎቶች ለማወቅ ዕድል ሰጥቶኛል፡፡ ጉዳዩ የማሻሻያ ጥያቄ አይደለም፡፡ አጠቃላይ የስርዓቱ/የእሽክርክሪቱ ችግር ነው፡፡ ስርዓቱ ሊጠገን ወይም ሊሻሻል የሚችል አይደለም፡፡ በጥቅምና በስርቆት መሰረት ላይ የቆመ ስርዓት ነው፡፡ ብዙ ቦታዎችን በተለያዬ ስም በማከማቸት ሂስ የወሰዱ አለቆች እዚያው ወንበር ላይ ተቀምጠው፣ ምንም የማያውቁ ሰራተኞቻቸውን በኪራይ ሰብሳቢነት ስም እያሸማቀቁ የሚገዙባት አገር ናት ኢትዮጵያ ማለት፡፡ 

አንዳንድ ጊዜ ዝርዝራቸው በጣም ብዙ የሆኑ ነገሮችን ጥቂት ለመዘርዘር እንኳን የምንቸገርበት ጊዜ አለ፡፡ የዝርዝሩ መብዛት የመዘርዘር ሙከራችንን አስቀድሞ ከንቱ ስለሚያደርግብን፡፡ የስርዓቱ ችግሮች እንዲህ ዓይነት ተስፋ አስቆራጭ ዝርዝሮች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡ ምናልባት አቦይ ስብሃት የእውነት የችግሩ ብዛት አልታያቸው ብሎ ከሆነ ለዚህ ነገር ሁለት ምክንያቶች ጎልተው ይታዩኛል፡፡ አንደኛው፣ ከውስጥ የመሆን ችግር ነው፡፡ በአንድ ስርዓት ውስጥ የስርዓቱ አካል ስትሆን የስርዓቱን ችግሮች ለመረዳት ይከብድሃል፡፡ አንድ ሰው ሽንት ቤት ውስጥ የሚኖር  ቢሆን የሽንት ቤቱን ሽታ ሊረዳው አይችልም፤ ይልቁንም ሽንት ቤቱን ሊጠቀም የሚመጣ ሌላ ሰው አፍንጫውን ይዞ ይሮጣል፡፡ ሁለተኛው፣ ራስን የማታለል ችግር ነው፡፡ ራሳችን የሰራናቸው ውሸቶች መልሰው ራሳችንን እንዲያሳምኑን መፍቀድ ነው፡፡ ራስን ማታለል ወይም ራስን መዋሸት ማለት ለሌሎች ከመዋሸታችን በፊት በውሸቱ ራሳችንን ማሳመን ማለት ነው፡፡ የአቦይ ስብሃት ንግግር በነዚህ ሁለት ምክንያቶች የተነሳ ካልሆነ ግን አቦይ ስብሃት አውቀውና አቅደው በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ንፁህ ተንኮል እየሰሩ ነው ማለት ነው፡፡ ይህን ጥያቄ ለአቦይ ስብሃት በማቅረብ በኩል አቤል አባተ ትተባበረኛለህ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ድርጅታችሁ መጠየቅን አልፎ አልፎ እንኳን የሚፈቅድ ከሆነ፡፡

በመጨረሻም አንድ ነጥብ ላንሳ፡፡ አንዳንድ ካድሬዎች የስርዓቱ አብዛኛው ችግር በበታች ሹማምንት የመጣ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ደርጎችም የሚሉት ይህንኑ ነበር፡፡ የደርግ የቀበሌ ካድሬዎች ህዝቡን የረሸኑት ስርዓቱ ስለፈቀደላቸው ነበር፤ የአሁኖቹ የቀበሌ ካድሬዎች ህዝብ የማይረሽኑት ስርዓቱ ስላልፈቀደላቸው ነው፡፡ የአሁኖቹ ፌዴራል ፖሊሶችና ልዩ ኃይሎች ሰው የሚፈጁት ስርዓቱ ስለፈቀደላቸው ነው፤ ህዝብን የሚበድሉና በሙስና የተጨማለቁ ሹማምንት አገሪቷን የሞሏት ስርዓቱ ስለፈቀደላቸው ነው፡፡ የደርግ ሹማምንት ይህንን ያክል በዘረፋ ተግባር ያልተሰማሩት ስርዓቱ ስላልፈቀደላቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ችግሩ የስርዓቱ ነው፡፡ ካንሰሩ የተሰራጨው ከላይ ጀምሮ ነው፡፡

ሃበሻ ሆይ! 

ጫንቃህ የተፈጠረው ቋጠሮ ሳይሆን ግፍ ለመሸከም ነውና በርታ፡፡ ዓይኖችህ ለእምባ፣ ጆሮዎችህ ለሙሾ፣ አፍህ ለእሪታ ተፈጥሯልና መከራህን ቻለው፡፡ ቅኔ ነህና የቅኔነት መዘዙን ትቋቋመው ዘንድ ፅናቱን ይስጥህ፡፡ እምቢ ካልክ ግን ሸክሙን እናወርድ ዘንድ አብረን እንጩህ፡፡

 ከዘፈን ያመለጡ ሰሚ ጆሮዎች ካገኘን፡፡
  

No comments:

Post a Comment