Sunday, October 18, 2015

ሰላማዊ ትግል

ሰላማዊ ትግል

በአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ የሰላማዊ ትግል አማራጭ ተቀባይነቱ ባዶ እየሆነ ይመስላል፡፡ ኢህአዴግ “ምንም አታመጡም” በሚል ትዕቢት አገሪቱን ያለፓርላማ እየገዛ ነው፡፡ ኦናው ቤት የተከፈተ ጊዜ አንዲት ሴትዮ ተኝታ የሚያሳይ ምስል የፌስቡክን ሜዳ ሞልቶት ነበር፡፡ እኔ ሴትዮዋ ዕድለኛ ካለመሆናቸው ውጭ የሴትዮዋ ጥፋት አልታየኝም ነበር፡፡ ጉዳዩ እንቅልፍን የመቋቋምና ያለመቋቋም ጉዳይ ነው፡፡ እኔም ብሆን ልተኛ እችል እንደነበር ይሰማኛል፡፡ ካሜራው ስላልያዛቸው እንጅ ሌሎች የተኙ ሰዎች አይጠፉም፡፡ በአጠቃላይ ሙሉ የፓርላማ አባላት ከእንቅልፍ ጋር እየታገሉ ጉባዔውን እንደጨረሱት መገመት አይከብድም፡፡ ስለዚህ ሴትዮዋ የትኛውን አጀንዳ እንዲከራከሩበት ነው መንቃታቸውን የፈለግነው? ያለቀለትንና የምታውቁትን ነገር ሰው ሲዘረዝርላችሁ እንቅልፋችሁ ካልመጣ እናንተ የእንቅልፍ በሽታ ተጠቂዎች ናችሁ፡፡ ሴትዮዋ ዕንቅልፋቸውን መቋቋም አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግም ግምገማ ካካሄደባቸው ግምገማው መሆን ያለበት ለምን በዘዴ እንዳልተኙ ነው፡፡ “መነፅር ለብሰው፣ ነጠላዎትን ጣል አድርገው ቢተኙ ምናለበት” ብሎ የሚገመግማቸው ይመስለኛል፡፡

የእኝህ ምስኪን ዕድለ-ቢስ ሴትዮ ጉዳይ የተነሳሁበትን ነጥብ አስረሳኝ፡፡ ወደነጥቤ ልመለስ፡፡

እንግዲህ ኢህአዴግ ምንም ዓይነት አማራጭ ሃሳብ የማይፈልግ ከሆነና ሁለንተናችንን አፍኖ መግዛት የሚፈልግ ፍፁም አምባገነን እየሆነ ከመጣ ሰላማዊ ትግል ምን ድረስ ያስኬዳል ነው ጥያቄው፡፡ እኔ የሰላማዊ ትግል አማራጭ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቃዋሚ ኃይሎችን ለስልጣን ያበቃል የሚል ሃሳብ ኖሮኝ አያውቅም፡፡ ነገር ግን ከወንበሩ ውጭ ያለውን ስልጣን ለመጠቀም ያስችላቸዋል ባይ ነኝ፡፡ ከወንበሩ ውጭ ያለው ስልጣን ምንድነው? ከወንበሩ ውጭ ያለው ስልጣን ብዙና ቀጥተኛ የፖለቲካ እርምጃ የሌለበት ነው፡፡ ለምሳሌ ኢህአዴግ ህዝቡን ጎሰኛ ማድረግ ይፈልጋል፤ ህዝቡ ጎሰኛ እንዳይሆን በኪነ-ጥበቡ፣ በሚዲያው፣ በትምህርት ቤቶች ወዘተ የመረባረብ ስልጣን በእጃቸው ነው፡፡ መንግስት በቀጥታ ሁሉንም ነገር ሊቆጣጠር ስለማይችል የመንግስት እጅ የሚያጥርባቸውን መንገዶች እየፈለጉ የህዝቡን አስተሳሰብ፣ የአገር ፍቅር፣ የፖለቲካ ባህል፣ ወዘተ. መቀዬር ይቻላል፡፡ ይህን ስናደርግም ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ መገንባት እንችላለን፡፡ ይህን የስልጣን ዘርፍ እንደኢህአዴግ ዓይነት የደንቆሮ ጥርቅም ቀርቶ ማንም በሳል ቡድን በአግባቡ ሊቆጣጠረው አይችልም፡፡ ስለዚህ የሰላማዊ ትግል አንዱና በአግባቡ ያልተነካው የትግል መስክ ይህ ነው፡፡

ሌላኛው መንገድ መንግስትን በተቻለ አቅም የማግባባትና ልቦናቸውን የማራራት መንገድ ነው፡፡ ይህ መንገድ በአግባቡ ተሞክሯል የሚል እምነት ፈፅሞ የለኝም፡፡ ከመንግስት አካላት ጋር በሰከነና በተረጋጋ መንገድ መነጋገር፣ ኢህአዴግ ውስጥ ካሉ ግለሰቦች ጋር በግል መገናኘትና መከራከር/መወያዬት፣ ተመሳሳይ የትብብር ስልቶችን መንደፍ፣ ወዘተ፡፡

ሶስተኛውና አዋጭነቱ ፈታኝ የሆነው ነገር ግን በኢትዮጵያ በአግባቡ ተሞክሯል ለማለት አሁንም የሚያስቸግረኝ መንገድ የጄን ሻርፕ መንገድ ነው፡፡ ይህ መንገድ ህዝቡ ለመንግስት የሚሰጠውን ትብብር እንዲነሳው በማድረግ መንግስትን ስልጣን የሌለው ባዶ ቀፎ የማድረግ ስልት ነው፡፡ ይሄን ስልት አምባገነኖች ከተቃዋሚዎች በላይ የሚያውቁት ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ከስር ከስሩ እየተከተሉ ሙከራውን ያከሽፉታል፡፡ በእኛም አገር አንዳንድ ሙከራዎች ቢኖሩም በቀላሉ ሲከሽፉ አይተናል፡፡ መክሸፋቸው ግን ከኢህአዴግ ነቄነት ብቻ ሳይሆን ከስልቶቹ አላዋጭነትም ይመነጫል፡፡ ስልቶቹን ወስዶ ከኢትዮጵያውያን ነባራዊ ሁኔታና የፖለቲካ ስነ-ልቦና አንፃር ማገናዘብና መስማማት ይጠይቃል፡፡ ይህን ስል ጉዳዩ በተግባር ሲወርድ ፈታኝ እንደሆነ አጥቼው አይደለም፡፡ ነገር ግን በአግባቡ ያልተሞከረን ነገር ውጤት እንዲሁ መቀበል ልክ ስላልሆነ ነው፡፡ “የወያኔን ምርቶች አትጠቀሙ” የሚል ድፍንና ስልት-አልባ ዘመቻ ማካሄድ የዚህን የትግል መንገድ ልክ አያሳዬንም፡፡

ማደማደሚያ

በአሁኑ የኢትዮጵያ አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ነጠላ የትግል አማራጮችን ማቅረብ የሚያስኬድ አይመስለኝም፡፡ ወንበር ለመገልበጥ የግድ ጠመንጃ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ነፍጥ ያነሱት ኃይሎች በዚህ በኩል ልክ ሳይሆኑ አይቀርም፡፡

ከጠመንጃው ውጭ ያለው መሰረታዊ የትግል አማራጭ ውድቅ ከተደረገ ግን ወንበር ተገልብጦም የማይስተካከል ነገር ይበዛል እላለሁ፡፡ ወንበር ለመገልበጥስ የጠመንጃው አዋጭነት ምን ድረስ ነው? ይህን ጥያቄ ራሱን ችሎ በሰፊው ማዬት የተሻለ ነው፡፡

ሰላማዊ ትግልን መጠቀም የኃይል አማራጩን መቃወም አይደለም፡፡ ፈፅሞ!
አሁንም ሰላማዊ ትግል ያስፈልገናል!!

***

ይህን ፅሁፍ ፅፌ እንደጨረስኩ ስልኬ አንቃጨለ፡፡
“ሄሎ፣ ሰበር ዜና ሰምተሃል?” … የወዲያኛው ድምፅ
“አልሰማሁም” … እኔ
“ዞን ዘጠኞች ተፈትተዋል”
በፈንጠዝያ ውስጥ ሆኜ ደስታውን ለማክበር ተቀጣጠርን፡፡ ወደዚያው እየሄድኩ ነው፡፡
እንኳን ደስ አላችሁ!
(ሰውን ይሄን ያክል ጊዜ ያለኃጢያቱ አስሮ የሚፈታ እንዲህ አይነት ደግ መንግስት ከቶ የታለ ፡) )
የኃይለማርያም ንግግር ታወሰኝ፡፡ ሽብርተኞች ናቸው ብሎም አልነበር!

No comments:

Post a Comment